ቻይና ግማሽ ቢሊየን ዶላር የኢትዮጵያን ዕዳ መክፈያ ጊዜ አራዘመች

Photo credit- PM office

የኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ፣ ቻይና ፣ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2024 ድረስ መክፈል የሚጠበቅባትን ግማሽ ቢሊየን ዶላር የኢትዮጵያን ዕዳ መክፈያ ጊዜ አራዘመች።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ አባልነቷ ተቀባይነት ባገኘበት የደቡብ አፍሪካው የጆሀንስበርግ የብሪክስ ጉባኤ ላይ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ቪ ጂንፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይት ነበር የብድር እፎይታው ይፋ የተደረገው። ሆኖም በወቅቱ ስለ ብድር እፎይታው እንጂ ፣ሀገሪቱ ከምን ያክል ብድሯ እፎይታን እንዳገኘች ግን አልተገለጸም ነበር ።

ኢትዮጵያ ከቻይና የተራዘመላት ብድር ወደ 500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ እንደሆነ ከተለያዩ ምንጮች መረዳት ተችሏል።

ላለፉት አመታት ሀገሪቱ በአማካይ እስከ ሁለት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በየአመቱ ለብድር ክፍያ አውጥታለች። ከዚህ አንጻር ሲታይ ከቻይና የተገኘው እፎይታ ኢትዮጵያ በዓመት ከምትከፍለው ብድር ሩቡን ያክል ይሆናል። 

የገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ አመት ያወጣው የመጨረሻው የመንግስትን የዕዳ ሁኔታ በሚተነትነው ሰነድ ላይ ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ብድር 28 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ይጠቅሳል። ከዚህ ውስጥ ከ13 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚሆነው ከቻይና የተገኘ ብድር እንደሆነ ይታመናል። ቤጂንግ የተጠቀሰውን የኢትዮጵያን ብድር መክፈያ ያራዘመችውም ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ጋር እያደረገች ያለው የዕዳ ሽግሽግ ውይይት እስኪጠናቀቅ ፋታ ለመስጠት መሆኑም መነገሩ ይታወሳል። የቻይና ብድር ወለዱ ከሌሎች አበዳሪዎች ከፍ ያለ በመሆኑ ጫና ፈጣሪ መሆኑ ይነገራል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ዕዳ የመክፈል ከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቃለች። የዕዳ መክፈል አቅምን የሚለኩ አለማቀፍ ኩባንያዎችም የሀገሪቱን ቁመና ዝቅተኛ ደረጃ ሰጥተውት ቆይተዋል። በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ሀገሪቱ ከአለም አቀፍ አበዳሪዎች የምታገኘው ፋይናንስ መቋረጡና የወጪ ንግድም በሚፈለገው ልክ አለማደጉ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ለመግባቷ በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው።

ኢትዮጵያ በቅርብ ወራት ውስጥ የዕዳ ማሸጋሸጊያ ተደርጎላት ተጨማሪ ብድር የማታገኝ ከሆነ በተለይ የፈረንጆቹ 2024 ከባድ የእዳ ክፍያ ጫና ውስጥ የምትገባበት አመት ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል። 

ቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት ኢትዮጵያ እስካሁን ስትከፍለው ከነበረው መደበኛ ብድር ባሻገር በፈንጆቹ 2014 በዩሮ ቦንድ የተበደረችውና የአስር አመት ዕድሜ ያለው አንድ ቢሊየን ዩሮ ሙሉው የሚመለስበት ዓመትም በመሆኑ ጫናው ከፍ ይላል።

ኢትዮጵያ ለአበዳሪዎቿ የጠየቀችው የዕዳ ሽግሽግ መዘግየቱን ስትገልጽ ቆይታለች። ከዚህም በተጨማሪ ሀገሪቱ ለሁለተኛው “የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” ለአበዳሪዎች የ12 ቢሊየን ዶላር ብድር መጠየቋ የሚታወስ ነው። 

የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ ) የኢትዮጵያን ዕዳ ሽግሽግ ጉዳይ ለመጨረስ የሀገሪቱ አበዳሪዎች የመክፈያ ጊዜዋን እንደሚያራዝሙ ቃል የገቡበትን ሰነድ እንዲሰጡ መጠየቁም ይታወቃል።

ምንጭ፦ [ዋዜማ]

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *