የዓለም አቀፍ ፍላጎትን ለማሟላት የነዳጅ ኢንዱስትሪው 14 ትሪሊየን ዶላር ያስፈልገዋል ተባለ

የዓለም አቀፍ ፍላጎትን ለማሟላት እስከ ፈረንጆቹ 2045 የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪው 14 ትሪሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል ሲል የነዳጅ ላኪ ሀገራት ድርጅት (ኦፔክ) ገለጸ።

የኦፔክ ዋና ጸሀፊ ሀይታም አል ጋይስ እንዳሉት፥ የዓለም አቀፍ የሃይል ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።

በዚህም በፈረንጆቹ 2045 የዓለም 30 በመቶ የሃይል ፍላጎት በነዳጅ ዘይት እንደሚሟላ አንስተው፥ ኢንቨስትመንቱ የእሴት ሰንሰለት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

በነዳጅ ዘይት ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸው፥ ሆኖም ከካርቦን ነጻ የሆነች ዓለምን ለመፍጠር የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን ማበረታታታችን ይቀጥላል ሲሉም ነው የተናገሩት።

በኦፔክ አባል ሀገራት በርካታ ፕሮጀክቶች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በታዳሽ ኃይሎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግም ምክክር እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

በፀሐይ፣ በኒውክሌር፣ በነፋስ እና በሌሎችም ታዳሽ ሃይሎች ኢንቨስት በማድረግ ረገድ እመርታ እየወሰዱ ያሉ መሪ የሆኑ አባል ሀገራት አሉም ነው ያሉት ዋና ጸኃፊው።

ኦፔክ ባለፉት 64 ዓመታት እንዳደረገው አሁንም በዘርፉ የሚደረጉ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲዎችን መደገፍ እንቀጥላለን ሲሉ መግለጻቸውን ከፒፕልስ ጋዜት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *