የኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ መድረክ የተመለከተ ውይይት በላሆር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተካሄደ

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከላሆር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የንግዱን ማህበረሰብ ተሳትፎ ለማበረታታት የኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ መድረክ አዘጋጅቷል።

ኢስላማባድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት የሚዘጋጀው የቢዝነስ መድረክ ከፈረንጆቹ ግንቦት 26 እስከ 31 ቀን 2024 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የንግዱ ማህበረሰብ በኢትዮ-ፓኪስታን የቢዝነስ መድረክ ላይ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ማዳበሪያ፣ መድሀኒት፣ ህክምና፣ ግብርና፣ ኬሚካል፣ ግንባታ፣ ቱሪዝም እና አይሲቲ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተከናወኑ ያሉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመጥቀስ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ስላሉ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎች አብራርተዋል።

የላሆር የንግድ ማህበረሰብም በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የንግድ ልኡካንን በመቀላቀል የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲቃኙ ጋብዘዋል።

አምባሳደሩ የፓኪስታን መንግስት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ህዝብ ያላትና ሰፊ የገበያ ማዕከል ከሆነችው አፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ አፍሪካን ተመልከቱ እና በአፍሪካ ተሳተፉ ፖሊሲን በማስጀመራቸው አመስግነዋል።

የፓኪስታን የንግድ ማህበረሰብ በአፍሪካ ካሉ አቻዎቻቸው ጋር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ አፍሪካ ግቡ በአፍሪካ ስሩ በሚል መርህ ያዘጋጀው መድረክ በእጅጉ እንደሚያግዝ ማንሳታቸውን ከኤንባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *