የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ስፔን ማድሪድ ከተማ በድጋሚ በረራ ጀመረ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሦስት ዓመታት ተኩል አቋርጦት የነበረውን ወደ ስፔን ማድሪድ ከተማ በረራ በድጋሚ ጀመረ።

አየር መንገዱ በሳምንት 4 ጊዜ ወደ ስፔን ማድሪድ በረራ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

አየር መንገዱ በረራ መጀመሩን አስመልክቶ ባዘጋጀው የማብሰሪያ መርኃ ግብር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ዲ ማኑኤል ሳላዛርን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በረራው በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ለሦስት ዓመት ከግማሽ ያህል ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል።

ዛሬ ዳግም በረራው መጀመሩ ለሁለቱ አገራት ሕዝቦች ትስስር መጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት የበረራ መዳረሻውን ወደ 135 አገራት ከፍ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ እየተለወጠ ባለው ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን መሰረተ ልማት ማስፋፊያ እንዲሁም ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ አውሮፕላኖችን እያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።

የበረራው መጀመር ስፔን ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ዲ ማኑኤል ሳላዛር በበኩላቸው የአየር መንገዱ ወደ ስፔን ማድሪድ ዳግም በረራ መጀመሩ የሁለቱ አገራት ትብብር ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *