የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2016 በጀት ዓመት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ከ20 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ዕቅድ መያዙን አስታወቀ።

ባንኩ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና በመስጠት እና በብድር የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ኢንተርፕራይዞች ለአገር ልማት የላቀ ሚና እንዲወጡ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል፡፡

እስካሁንም በአራት ዙር የሰጠውን የሥልጠና መስፈርት አሟልተው የብድር ጥያቄ ላቀረቡ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር መስጠቱን ጠቅሷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የባንኩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የአብሥራ ከበደ፤ እንደጀርመን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ጃፓን ያሉ መሰል አገራት የባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትነት መነሻ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው ብለዋል።

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በማቅረብና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዘርፍ መሆኑን ገልጿዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በእውቀትና ክህሎት የሚመሩ ጠንካራ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ ባንኩ ተከታታይ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት አራት ዙር ሥልጠናዎችም 133 ሺህ ዜጎች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

ሥልጠናውን ለመውሰድ ተመዝግበው ከሚጠባበቁ 320 ሺህ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች መካከል በበጀት ዓመቱ እስከ 75 በመቶ ያህሉን አሰልጥኖ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አብራርተዋል።

ሥልጠና የወሰዱ የብድር አገልግሎት ፈላጊ ዜጎችም የገበያ አዋጭነት ሃሳባቸውን ለባንኩ ማቅረብ እንዳለባቸው የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ባንኩም ብድር በመስጠት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይሰራል ብለዋል።

በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ አንቀሳቃሾች 20 ከመቶ የስራ ማሟላት ያለባቸው ሲሆን ባንኩ የቴክኒክና የምክር አገልግሎትን ጨምሮ 80 ከመቶ ብድር እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ስልጠናውን ተከታትለው የንግድ እቅዳቸውን ለባንኩ ላቀረቡ ዜጎች 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር መስጠቱንም ጠቅሰዋል።

በዚህ የብድር ድጋፍ ወደስራ የገቡ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ራሳቸውንና አገርን ተጠቃሚ ወደ ማድረግ መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም የባንኩን ስልጥና በአግባቡ ለተከታተሉና ዝርዝር የንግድ ስራ እቅድ ለሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞች 20 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ብድር ለመስጠት መታቀዱን ይፋ አድርገዋል።

የባንኩ የፋይናነስ አካታችነትን ለማረጋገጥ አማራጮችን እያሰፋ መሆኑን ገልጸው፤ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ዜጎች የብድር አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ የኢንተርፕራየዝ አንቀሳቃሾች ማመልከቻ፣ የስልጠና ምስክር ወረቀት፣ ፍቃድ፣ የመስሪያ ቦታ፣ የውክልና ስልጣን፣ የዋጋ ማሳወቂያ ደረሰኝ፣ የቅድመ ስራ ታሪክ፣ የግብር ግዴታ፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናትና ደብዳቤ፣ አስተዳደር፣ የድርጅት/ግለሰብ የመዋጮ ምንጭ፣ የተሳትፎ ምስክር ወረቀት፣ ዝርዝር የንግድ ስራ እቅድ ወይም የአዋጭነት ጥናትን ማሟላት አለባቸው።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላለፉት 115 ዓመታት የአገርን ኢኮኖሚያዊ እድገት በመደገፍ ላይ የሚገኝ የፖሊሲ ባንክ መሆኑ ይታወቃል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *