የአገር ውስጥ በረራ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት እየተጠናቀቀ ባለው በጀት አመት የአገር ውስጥ ተጓጓዦች ቁጥር 3.5 ሚሊየን ይደርሳል፤ ይህ መጠን ከ2015 በጀት አመት አንጻር የ34.6 በመቶ ጭማሪ የሚኖረው ነው።

በቀደመው አመት በአገር ውስጥ በረራ የተስተናገዱት ተሳፋሪዎች 2.6 ሚሊየን እንደነበሩ አቶ መስፍን አስታውሰዋል።

አየር መንገዱ እየሰፋ ያለውን የደንበኞች ቁጥር ታሳቢ በማድረግ የቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ አሁን በአመት ማስተናገድ ከሚችለው 25 ሚሊየን መንገደኞች ከ4 እጥፍ በላይ ማስተናገድ የሚችል አየር ማረፊያ እና ማስተናገጃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ሆኖም ይህ ማእከል የአለም አቀፍ እና በተወሰነ መልኩ የጭነት ማስተናገጃ ሆኖ የሚሰናዳ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።

የቦሌ አየር ማረፊያ እያደገ የመጣውን የአገር ውስጥ በረራ በማሰተናገድ ይቀጥላል ያሉት አቶ መስፍን፣ የጥገና እና የጭነት ማእከሉም በቦሌ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ ለአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ የአየር መንገዶች የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጥ ይታወቃል። ይህንኑ ስራ ለማስፋት ተጨማሪ የመለዋወጫ ማስቀመጫ እና የጥገና ማእከል እየሰራ ሲሆን እስከመጪው ታህሳስ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ እጅግ ዘመናዊ የጭነት ማእከል የገነባው አየር መንገዱ ዋነኛ የችነት ማእከሉን በቦሌ እንደሚቀጥል ነው አስተዋውቋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው አዲስ የአየርመንገድ ከተማ ከቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ ጋር በፈጣን ባቡር እንደሚገናኝ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ካፒታል

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *