የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ከአውሮፓ የፈጠራ ባለቤትነት ቢሮ ጋር የትብብር ሥምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን እና የአውሮፓ የፈጠራ ባለቤትነት ቢሮ ሦስተኛው ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የሥራ ዕቅዳቸው ላይ በትብብር ለመሥራት ተፈራርመዋል።

ሥምምነቱ ከፈረንጆቹ 2023 እስከ 2025 የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል እና የአውሮፓ የፈጠራ ባለቤትነት ቢሮ ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ካምፒኖስ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ከተሳተፉ ልዑካን ቡድኖች መካከል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ፎዚያ አሊዪ (ዶ/ር)፥ ባለሥልጣኑ የሁለት ዓመታት የሥራ ዕቅድ መፈራረሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የያዘውን ብሔራዊ የፈጠራ ኅጉን የማሻሻል ሥራ ለማጠናቀቅ አቅሙን እንደሚያጠናክርለት ገልጸዋል።

ፎዚያ አሊዪ (ዶ/ር) የትብብር ሥምምነቱ የፈተና መመሪያዎችን በማዘጋጀቱ ሂደት እንዲሁም ወደ ፓሪስ ሥምምነት ለመግባት የቴክኒክ ድጋፍ በማግኘት ረገድ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የሁለቱን አካላት የአጋርነት ሥምምነትንም አድንቀዋል።

በሁለቱ አካላት ሥምምነት መሠረት በፈረንጆቹ ኅዳር 8 እና 9 በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፎዚያ አሊዪ (ዶ/ር) ፣ በፍትኅ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን እንዲሁም በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል የተመራ ልዑክ የአውሮፓውን የፈጠራ ባለቤትነት ቢሮ መጎብኘቱ እና በሚሠሯቸው ሥራዎች ላይ መወያየታቸውም ተጠቁሟል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *