የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ኬሚካልና የብረታብረት ማምረቻ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ኬሚካልና የብረታብረት ማምረቻ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎች እንዲያጠናክሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትር ዴኤታው በቻይና የዓለም አቀፍ ንግድ ግንኙነቶች ማስተዋወቂያ ካውንስል ምክትል ሊቀመንበር ዣንግ ዣኦግንግ ከተመራው የቻይና የንግድ ልኡክ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ለልዑኩ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንትና የንግድ እድሎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ኬሚካል፣ የአፈር ማዳበሪያና የብረታ ብረት ማምረቻ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለሀብቶቹ በዘርፎቹ መዋእለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂክ አጋርነት ለማሳደግ የተደረሰውን ስምምነት እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለቻይና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን አስታውሰው ቻይናም ለኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ወሳኝ ምንጭ መሆኗን አስገንዝበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና ጋር የንግድ ለንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው ባለሀብቶቹ በኢንዱስትሪና ነጻ የንግድ ኢኮኖሚ ዞኖች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለውን ምቹ ሁኔታ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት የቻይናውን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በመቀላቀል ቀዳሚውን ስፍራ እንደምትይዝ አስታውሰው የቻይና ባለሀብቶች ትልቅ ሚና በሚጫወቱበት በዘላቂ ልማት፣ አህጉራዊ የትራንስፖርት ትስስር፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች ካሉት እድሎች ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላት አብራርተዋል።

የቻይና የዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነት ማስተዋወቂያ ካውንስል ምክትል ሊቀመንበር ዣንግ ዠኦግንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገራትን በመቀላቀሏ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሊቀመንበሩ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሮች ለማጠናከር ያላትንት ፍላጎትም መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *