የስቶክ ገበያ እንዴት ይሰራል?

መደበኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመገበያያ ገበያዎች ሊኖሩ ይችላሉ (የክፍያ ስርዓታቸው በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ሊያልፍ ይችላል)። ነገር ግን የስቶክ ገበያ (Stock Market) ካምፓኒዎችን ለበርካታ ህዝብ የመሸጥ እና የመግዛት ሂደት የሚመራበት የገበያ አይነት ነው።

ስቶክ ገበያን ለመጀመር በአውሮፓ የቀደሙ ሀገራት ቢኖሩም እንግሊዛውያን የስቶክ ገበያን 1773 (የለንደን የስቶክ ገበያ/London Stock Exchange በቡና ቤት/በካፌ ውስጥ በመገናኘት ግብይት ጀመሩ፡፡ በአሜሪካ የመጀመሪያው የስቶክ ገበያ የተቋቋመው በፊላደልፊያ በ1790 ሲሆን ከ2 ዓመት በኋላ 1792 ገበያው ወደ New York’s Wall Street ተዘዋውሯል።

በመደበኛ ገበያ ገንዘብ/ብር መገበያያ ሆኖ ሲያገለግል በስቶክ ገበያ ግን መተማመኛ ወረቀት/ቦንድ መገበያያ ሆኖ ያገለግላል። የስቶክ ገበያ በሂደት እየዘመነ በመምጣት በወቅቱ ለገዢ እና ለሻጭ ይሰጥ የነበረው ሰርተፍኬት ሲሆን አሁን ላይ ወደ ዲጂታል ሰነድነት ተዘዋውሯል።

ይህንን ድርጅትን ለበርካታ ሰዎች የማሻሻጥ ስራ የሚሰሩ በህግ እን በደንብ የሚቋቋሙ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው የስቶክ አሻሻጮች/Stock Exchanges ይባላሉ (ለምሳሌ በአሜሪካ መደበኛ የፋይናንስ ሁኔታን ከሚቆጣጠሩት በተጨማሪ ራሱን የቻለ Securities and Exchange Commission አለ)፡፡ የተቆጣጣሪ ድርጅቶች ሚና ለተገበያዮች በቂ ጥበቃ መሰጠቱን ማረጋገጥ፤ ፍትሃዊ ገበያ መኖሩን ማረጋገጥ፤ ጤነኛ የካፒታል ዝውውር መኖሩን ማረጋገጥ፤ ወዘተ ነው።

በዓለም ላይ ታዋቂ የመንግስት፤ የመንግስት እና የግል እንዲሁም የግል የስቶክ አሻሻጭ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን! በዓለም ላይ ግዙፎቹ የስቶክ ገበያዎች መካከል ዋናዎቹ የአሜሪካኖቹ (New York Stock Exchange እና NASDAQ)፤ የጃፓኑ (Tokyo Stock Exchange)፤ የቻይናዎቹ (Shanghai Stock Exchange እና Hong Kong Stock Exchange)፤ የእንግሊዙ (London Stock Exchange) ናቸው።

በኢትዮጵያ ስቶክ (ሰነደ መዋለ ንዋይ) ለማገበያየት የሚቋቋሙ ድርጅቶች የ25 ከመቶ የመንግስት እና 75 ከመቶ የግል ባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ይሆናሉ።

የስቶክ ገበያ የንብረት ሻጭ እና ገዢን የማገናኘት እና ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያደርጉ ተቋማት ናቸው (እንደቀጥተኛ ማለትም ሻጭም ገዢም ቀርበው እንደሚገበያዩበት የገበያ አይነት ይቆጠራል)፡፡ ይህ ገበያ አዋጪ ዋጋ፤ በቀላሉ ክፍያ የመለዋወጥ እና ታማኝነት ያላቸው የነጻ ገበያ ባህሪ አላቸው።

የስቶክ ገበያ እንዴት ይሰራል?

ካምፓኒዎች ላላቸው ድርጅት ተጨማሪ ካፒታል በሚፈልጉ ጊዜ ወይም አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ምን ያህል ካፒታል እንደሚፈልጉ እና የት እንዲሸጥላቸው እንደሚፈልጉ ለነዚህ ስቶክ አገበያዮች ያሳውቃሉ። ከዚያ እነዚህ የስቶክ አገበያዮች ባላቸው ፕላትፎርም በተባለበት ቦታ በሙሉ አክሲዮኑን ለሽያጭ በማቅረብ ከገዢ ገንዘብ በመቀበል የድርጅቱን ድርሻ ስለመግዛቱ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጣሉ ማለት ነው።

በስቶክ ግብይት ወቅት የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ባለ ቁጥር ሻጭ ድርጅትም ሆነ አክሲዮን ገዢ የአክሲዮን ትርፋቸው ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል! ይህንን በሙሉ እነዚህ የአክሲዮን ገበያዎች ይመሩታል (አንድ ሰው አንድ አክሲዬን ቀድሞ አክሲዮኑን ከገዛ ሰው ከገዛ ሁለተኛ ገበያ ይባላል! ምክንያቱም ከድርጅቱ በቀጥታ ሳይሆን ከገዢ ስለገዛው ነው። የአክሲዮን ገበያዎቹ ለሰሩበት ከሻጭ እና ከተሳታፊዎች የአገልግሎት ክፍያ ያገኛሉ።

በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት በኢትዮጲያ የስቶክ ህግ እና ስርዓት በአግባቡ ስላልነበር በዚህ ወቅት ባንኮች በውክልና የተለያዩ አክሲዮኖችን እያሻሻጡ እንዳሉት ማለት ነው።

የስቶክ ገበያዎች መኖር ሻጭም ሆነ ገዢ ስለገበያው እና ስለፍትሃዊ የመሸጫ ዋጋው በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በስቶክ ገበያ ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉት የስቶክ ገበያ አመቻቾቹ፤ ሻጮች፤ ገዢዎች እና ደላሎች (ለምሳሌ፦ አንዳንዶች እንደቋሚ ቁስ አክሲዮኖችን ገዝተው ሲወደድ የሚሸጡ አሉ!) ናቸው።

የስቶክ ገበያ መኖር ትንንሽ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ወደ ትርፍ ሊያመጡ ወደሚችሉ የአክሲዮን ገበያ በመግባት ትርፍ እንዲያገኙ፤ የካፒታል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች/ድርጅቶች ካፒታል በመፍጠር ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እና በኢኮኖሚው ውስጥ ፈጣን የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲኖር የማድረግ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሲኖራቸው የውጪ ባለሃብቶችን ከመሳብ በተጨማሪ ከተፈጠረው የካፒታል እድገት በሚፈጠር ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚው የስራ እድል እና የግብር ገቢው እንዲያድግ ያደርጋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *