የሙያ ደኅንነትና ጤንነትን ለመጠበቅ አዲስ የአሠራር ሥርዓት እየተዘረጋ ነው

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ዴስክ ኃላፊ ጥዑመእዝጊ በርሄ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መከላከልን መሰረት ያደረገ አጠቃላይ የሙያ ደኅንነትና ጤንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል አዲስ አሠራር እየተዘረጋ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አጠቃላይ የሥራ ላይ ደኅንነትን ከማረጋገጥ አኳያ ከ12 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የጎንዮሽ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ገልጸው፤ ስምምነቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ከዚህ በፊት ያልነበራቸው የየራሳቸው ፖሊሲ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

“ሀገር አቀፍ የሥራ ደኅንነትና የሙያ ጤንነት ፖሊሲ እስከዛሬ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ፖሊሲ ብቻ ሆኖ ነው የቀረው።” ያሉት ኃላፊው፣ ፖሊሲው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የየራሳቸውን ፖሊሲ ማውጣት አለባቸው ቢልም ሳያወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ጥዑመእዝጊ ገለጻ፣ ስምምነቱን ከፈረሙት 12 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር ባለፈው ዓመት በጋራ መሥራት በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር ተደርጎ የጋራ ዕቅድ ወጥቷል።

እስካሁንም ከስምንቱ ጋር የራሳቸውን ፖሊሲ እንዲያዘጋጁ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል ያሉት ኃላፊው፤ የፖሊሲ ዝግጅቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በሥራቸው ባሉት ዘርፎች ደኅንነቱና ጤንነቱ የተጠበቀ የሥራ ቦታ እንዲገነባ ከማድረግ አኳያ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የሙያ ደኅንነትና ጤንነትን ተቆጣጣሪ ከ400 እስከ 500 የሚገመት መሆኑንና ከሀገሪቱ ሕዝብ አንፃር ቁጥሩ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በቁጥጥር ረገድ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ በዚህ ዓመት በቢኤ ዲግሪ ለተመረቁ አንድ ሺህ ተማሪዎች የሶስት ዙር ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በእያንዳንዱ የሥራ ቦታ ላይ ከአሰሪውና ከሠራተኛው በተውጣጡ አባላት የሥራ አካባቢ የሥራ አመራር ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተናግረዋል።

በኮሚቴው ውስጥ አሠሪም ሠራተኛውም እኩል መብት እንደሚኖራቸው አመላክተው፣ ኮሚቴው በተወሰነ ጊዜ እየተገናኘ ስለሥራ አካባቢ ደኅንነትና ጤንነት እንዲወያይ ይደረጋል። በሥራ አካባቢ የደረሱ አደጋዎችንም በዝርዝር ይገመግማል ብለዋል።

አክለውም፣ ይሄን ለማስፈጸም የሚያስችል መመሪያ ባለፈው ዓመት መውጣቱን አውስተው፣ መመሪያውን መሰረት በማድረግ ደንብ እያዘጋጀንና የአሠራር ሥርዓት እየዘረጋን ነው ብለዋል።

እየተዘረጋ ያለው አዲስ አሠራር የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ አጠቃላይ የሥራ ላይ ደህንነትና የሙያ ጤንነትን ማስከበር ያስችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመላከቱት ኃላፊው፤ በቅድሚያ ግን አሠሪዎችና ሠራተኞች ግንዛቤው እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ መሥራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ምንጭ፦ ኢፕድ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *