ኮርፖሬሽኑ ከ11 የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ጋር ለመስራት ተስማማ

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከ11 የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ጋር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና ባለሀብቶች ተፈራርመዋል።

ባለሃብቶቹ ኮርፖሬሽኑ ካሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል በአምስቱ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ገብተው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት።

በዚህም በመቀሌ፣ ጅማ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በእያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ኩባንያዎች የሚገቡ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ ሁለት ባለሀብቶች ደግሞ በባህርዳር እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሳሉ ተብሏል።

ባለሃብቶቹ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ፣ በመድሀኒት እንዲሁም በፕላስቲክ ማምረት ዘርፍ ይሰማራሉ ተብሏል።

11 ባለሀብቶች በድምሩ ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን÷ 31 ሺህ ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድና 4 ነጥብ 5 ሄክታር የለማ መሬት ተረክበው ወደ ስራ እንደሚገቡም ተገልጿል።

ስምምነት ከተፈራረሙት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ሲሆኑ÷ 50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የሆነ የገበያ ትስስርና 5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የስራ እድል የሚፈጥሩ ይሆናል ነው የተባለው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ÷ ስምምነቱ እነዚህ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም በፀጥታ ችግር ምክንያት ስራ አቁሞ የቆየውን የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *