አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለአገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል- አቶ መላኩ አለበል

አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለአገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

ሚኒስትሩ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውና የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ለአምራች ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት መሰጠቱ ለዘርፉ መሻሻል አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ መጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዓለም አቀፋዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል።

አዲሱ ፖሊሲ ላለፉት 20 ዓመታት ሲተገበር የቆየው ፖሊሲ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በሚደፍን መልኩ እንዲሁም የቴክኖሎጂ እድገትን፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ አድርጎ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የግብዓት፣ የኃይልና የፋይናንስ ተግዳሮች ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በተለይም በፋይናስ አቅርቦት ላይ የነበረውን ችግር ለመፍታት ባንኮች ከፍተኛውን የብድር መጠን ለግል ዘርፉ እንዲሰጡ መደረጉ ችግሩን እያቃለለ ነው ብለዋል።

ለአብነትም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ለኢንዱስትሪዎች 266 ሚሊዮን ዶላር ብድር መቅረቡን ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት አቁመው ከነበሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል፤ ድጋፎችን በማድረግ 376ቱ ወደ ምርት መግባታቸውንም ነው አቶ መላኩ የገለጹት።

የኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅም በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 46 በመቶ አሁን ላይ ወደ 56 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የመስሪያ ቦታ ከወሰዱ 127 አምራቾች ግማሹ የአገር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸው፤ አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለአገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

ገቢ ምርቶችን ለመተካት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፊ ስራ መሰራቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የመንግስት ተቋማት የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ ከማድረግ ጀምሮ ማበረታቻዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የግል ዘርፉ ከመንግስት የሚደረጉለትን ድጋፍና ማበረታቻዎች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ ማዋል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

አቶ መላኩ አያይዘውም ባለፉት አምስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች 131 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸው፤ ገቢው ከተላከው ምርት አኳያ ተመጣጣኝ አለመሆኑንም አንስተዋል።

ለዚህ ደግሞ አንዳንድ ምርቶች ላይ የመሸጫ ተመን አለመውጣቱ፣ የዓለም ገበያ መዋዠቅ፣ ምርቶቹ ላይ በቂ እሴት አለመጨመርን በምክንያትነት አንስተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *