አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የቡና ምርት መሰብሰቡን አስታወቁ

በ2016 የምርት ዘመን 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የቡና ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን እና እስካሁን ከ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ፡፡

አፈፃፀሙ በምርት መጠንና ፍጥነት የተቀመጡት ግቦች እየተሳኩ መሆናቸውን ያመለክታል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ከግብርናው ዘርፍ ዓላማዎች አንዱ የወጪንግድን ማሳደግ መሆኑን ጠቁመው ÷ ይህንን ግብ ከማሳካት አንፃርም የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ ግንባር ቀደም ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

በቡና ምርት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የቡና ጥራት ጥበቃና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ዓመት ለገበያ ከሚቀርበው ቡናም 75 በመቶው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን የጥራት ደረጃ እንዲይዝ መታቀዱንም ነው የጠቆሙት፡፡

ይህንን እቅድ ለማሳካትም ከክልል እስከ ቀበሌ የቡና ምርት ጥራት አጠባበቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች መካሄዳቸውንና አቅጣጫም መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የቡና ጥራት ጥበቃና ገበያ በተለያዩ ዘርፎችና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንዲመራ ከክልል እስከ ወረዳ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ነው የተናገሩት።

የዓመቱ የቡና ምርት ለቀማ፣ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መጀመሩን ገልጸው÷ ከ 15 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ የቡና ማድረቂያ አልጋ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *