በጸረ ሙስና ዘመቻ ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች ቁጥር 640 መድረሱ ተገለጸ::

የፌደራል መንግስት በህዳር ወር ላይ ላቋቋመው የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ በደረሰው ጥቆማ መሰረት፤ በሙስና ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች ቁጥር 640 መድረሱ ተገለጸ። የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴው 226 ሺህ ካሬ ሜትር ገደማ መሬት ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ይህ የተገለጸው የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች የተቋቋሙት የጸረ ሙስና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ሐሙስ የካቲት 30፤ 2015 በስካይ ላይት ሆቴል እያደረጉት ባለው የግምገማ መድረክ ነው። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር እና የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴው ከደረሱት 759 ጥቆማዎች ውስጥ በ175 ያህሉ ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ምርመራውን ተከትሎ በተከፈቱት 81 የክስ መዝገቦች የተከሰሱ ሰዎች ብዛት 640 መድረሱን አቶ ተመስገን አስታውቀዋል። በደረሱት ጥቆማዎች መሰረት 2.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት “የህዝብ እና መንግስት ንብረት” በሙስና ጉዳት እንደደረሰበት መታወቁን ተናግረዋል። የክልል ጸረ ሙስና ኮሚቴዎች ግኝት ጉዳት እዚህ ላይ ሲጨመር ጉዳቱን ከዚህ ሊጨምር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሙስና “የሀገር ደህንነት ስጋት” መሆኑን በማስታወቅ ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴ ያቋቋሙት ከሶስት ወር ገደማ በፊት ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ይህ ኮሚቴ “መንግስት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የማስተባበር” እና የሙስና “ተዋንያን” እየለየ ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነት ያለው ነው። የዚህን ኮሚቴ መቋቋም ተከትሎ፤ የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮችም ተመሳሳይ አይነት ቅርጸ ያላቸው ኮሚቴዎችን እንዳዋቀሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *