በጂቡቲ ወደብ ላይ የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈ ተሸከርካሪዎች በባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ተጓጉዘው ወደ አገር ከገቡ በኋላ ድሬዳዋ ደረቅ ወደብ እንዲቆዩ ተወሰነ።

ሚኒስቴሩ፦
➡️ ለባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት
➡️ ለጉምሩክ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ የተሽከርካሪዎቹ አስመጪዎች በሚያቀርቡት መረጃ መሠረት፣ በየወቅቱ በጂቡቲ ወደብ የተከማቹ ተሽከርካሪዎችን መጠንና የቆይታ ጊዜ ከጂቡቲ ወደብ ባለሥልጣንና ከጉሙሩክ ኮሚሽን እንዲሰበሰብ አዟል።

የባህር ትራንስፖርት የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወደብ ፎርማሊቲ አሟልቶ ተገቢ ክፍያ በመፈጸምና በድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ማከማቻ ሥፍራ በማዘጋጀት ተለዋጭ ውሳኔ እስኪሰጥ በራሱ ኃላፊነት እና በራሱ ወጪ ተሽከርካሪዎቹን እንዲያቆይ ተወስኗል።

የጉምሩክ ኮሚሽን በበኩሉ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሚሰጠው የደብዳቤ ዋስትና፣ ተሽከርካሪዎቹ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው እንዲጓጓዙ የትራንዚት ፈቃድ እንዲሰጥ የገንዘብ ሚኒስቴር አሳስቧል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ለጉምሩክ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ በጂቡቲ ወደብ ተከማችተው የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ድሬዳዋ ደረቅ ወደብ እንዲጓጓዙ መወሰኑን አስታውቆ፣ በውሳኔው መሠረትም አስመጪዎች ንብረቶቻቸውን ወደ ደረቅ ወደብ እንዲያስገቡ አሳስቧል።

ነዳጅ ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ጫና ለመቀነስ በሚል በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዳይገቡ ውሳኔ መተላለፉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር በስፋት እንዲገቡ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ መደረጉን መግለጹ አይዘነጋም።

ሪፖርተር ጋዜጣ ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ምንጭ አገኘሁት ባለው መረጃ፣ አሁን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የተባሉት የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ከዕግዱ በፊት የተገዙ ናቸው።

በውጭ ምንዛሪና በፍራንኮ ቫሉታ ምክንያት በጂቡቲ ወደብ እንዲቆዩ የተደረጉ መሆናቸውን፣ ውሳኔው የተላለፈው ለተሽከርካሪዎቹ የሚከፈለው የወደብ ኪራይ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑ ተመላክቷል።

ተሸከርካሪዎቹ ድሬዳዋ ደረቅ ወደብ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፣ ሰነድ ያላቸው የተሽከርካሪ አስመጭዎች ድርጅቱ ያወጣውን የታክስና የመጓጓዣ ወጪ በመክፈል መረከብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተሽከርካሪ አስመጪ “የአንድ ዓመት የወደብ ኪራይና የመጓጓዣ ወጪዎችን በመክፈል ተሽከርካሪዎቹን ቢረከቡ ገበያ ውስጥ ዋጋቸው ስለሚንር ሥጋት ገብቶናል” ብለዋል።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *