በኢትዮጵያ የላዳ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠምና ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የሩሲያው ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ላዳ እና ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት እና ለመገጣጠም የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ  እና የላዳ የወጪ ንግድ ዳይሬክተር፣ የሽያጭ እና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሊያ ሳቪኖቭ ናቸው።

አምባሳደር ሱሌማን በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሩሲያ ባለሐብቶች በተለይም በማዕድን፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ዛሬ በተፈረመው ስምምነት መሰረትም÷ ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የላዳን ያልተጠናቀቁ ምርቶች በመገጣጠም ሥራ የሚጀምር ይሆናል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ግብዓቶችን በማስመጣት ተሽከርካሪዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብም ነው ያስታወቁት።

ኢሊያ ሳቪኖቭ በበኩላቸው÷ በርካታ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን  ተናግረዋል።

የሩሲያ ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረምም ከነገ በስቲያ እንደሚካሄድ ጠቁመው÷ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ አመላከትዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *