በቮልስ ዋገን አይዲ ሲሪየስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሳ::

በቮልስ ዋገን አይዲ ሲሪየስ (ID Series) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ተጥሎ የነበረው እገዳ የተነሳ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ከቻይና ተገጣጥሞ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው የጀርመን ምርት የሆነው ቮልስ ዋገን ተሽከርካሪ ባትሪው ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጋር የሚጣጣም አይደለም በሚል በቀረበው ቅሬታ መሠረት የማስገቢያ ፈቃድ ተከልክሎ ቆይቷል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪና ተሽከርካሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አበራ ሞሲሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጀርመን መንግሥት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ቮልስ ዋገን ተሽከርካሪ እንዳይገባ ተደርጎ ቆይቷል፡፡

ደብዳቤው የተሽከርካሪዎች ባትሪ ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጋር የማይጣጣም እንዲሁም የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ ፈቃድ አልሰጠም የሚል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከባትሪው ጋር ተያይዞ የቀረበውን አቤቱታ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስጠንተን፤ ባትሪው ምንም ችግር የሌለበትና ለኢትዮጵያ የአየር ንብረትም ተስማሚ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በተሽከርካሪው ላይ ያለው ባትሪ ሙሊት ጊዜ ከዜሮ እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዲሁም በሥራ /ዲስቻርጂንግ/ ወቅት ከ20 እስከ 60 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህ የሙቀት መጠን ላይ ያለ ባትሪ ጥሩ የሚባልና በኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ ለመሥራትም ምንም ዓይነት ችግር የማይፈጥር መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

የቮልስ ዋገን ተሽከርካሪ ፈሳሽ የባትሪ ሙቀት መቆጣጠሪያ የሚጠቀም በመሆኑ ከሌሎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተሻለ በተለያዩ የአየር ንብረት ሁኔታ የመሥራት አቅም እንዳላቸውም አብራርተዋል።

የጀርመን መንግሥት ያቀረበው ለኢትዮጵያ ፈቃድ አልሰጠሁም ለሚለው ጥያቄም “ኢትዮጵያ በቻይና የተገጣጠሙትን በሦስተኛ ወገን ማምጣቷን ገልጸው፤ መነጋገር የሚችለው ከቻይና ጋር እንጂ ከእኛ ጋር አይደለም” ብለዋል፡፡

በመሆኑም አስመጪዎች ሕጋዊውን አሠራር ተከትለው የቮልስ ዋገን ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይችላሉ ብለዋል፡፡

በቻይና የሚገጣጠሙ እነዚህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከሀገራችን የአምራች ቀጥታ ተወካይ እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡

የተሽከርካሪዎቹ አስመጪዎች ሙሉ መረጃና ዋስትና መኖሩን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ውጤት መሠረት አገልግሎት የተጀመረ በመሆኑ፤ እነዚህን ክፍተቶች ማሟላት የሚችል አስመጪ ድርጅት የማስገቢያ ፈቃዱን መውሰድ ይችላል ብለዋል፡:

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *