በመዲናዋ ለ562 ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጠ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ግብር በታማኝነት ለከፈሉ ግብር ከፋዮች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እና የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አደም ኑሪን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ተሸላሚዎቹ በ2015 በጀት ዓመት ግብርን በታማኝነት በመክፈልና የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ለከተማዋ ዕድገት እስተዋፅኦ ያበረከቱ መሆናቸው ተገልጿል።

ዕውቅና እና ሽልማት ከሚበረከትላቸው ግብር ከፋዮች ውስጥም 104 የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ተሸላሚዎች የሚጠበቅባችሁን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈላችሁ ድርብ ኩራትና ደስታ ሊሰማችሁ ይገባል ብለዋል።

ግብርን መሰወር ከእናት መቀነት እንደመስረቅ ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ ድርጊቱ ነፃነት እና ክብርን የሚገፍ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

“ግብራቸውን በታማኝነት ለከፈሉ ሀገር ወዳዶች ዕውቅና ሰጥተን በአደባባይ እንዳከበርነው ሁሉ አሰራራችንን እና አገልግሎት አሰጣጣችንን በማዘመን ሕገ ወጦችን በህግ ተጠያቂ እናደርጋለን” ሲሉም ገልጸዋል።

አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው÷በከተማዋ ለሚታዩ ፕሮጀክቶችና መሠረተ ልማቶች መሻሻል የግብር ከፋዮች አሻራ ትልቅ መሆኑን አውስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ገቢ ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው÷በ2015 በጀት ዓመትም 109 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *