የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ከቻይና አለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር ጋር በሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ላይ ተወያዩ፡፡

የካቲት 27 / 2015 ዓ.ም – የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በቻይና አለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር በሚስተር ሊ ዚያንግ ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በቀጣይ ስለሚከናወነው የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር በጽ/ቤታቸው ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ወቅት ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የቻይና አለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በሀይል ማመነጫና በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ግንባታዎች ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ግዙፍ የቻይና ካምፓኒ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ከዚህ ግዙፍ ካምፓኒና ከሌሎችም የቻይና ኢንቨስተሮች ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

የቻይና አለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀ መንበር ሊ ዚያንግ በበኩላቸው ቡድኑ በኢትዮጵያ የተከዜ ሀይል ማመንጫን፣ የፊንጫ አመርቲ ነሽ ሀይል ማመንጫን፣ ገናሌ ዳዋ 3 ሀይል ማመንጫንና የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን አውስተው ቡድኑ በቀጣይነትም በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም በታዳሽ ሀይሎች ኢንቨስትምንት የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል፡፡

የቻይና አለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ከቻይና ግዙፍ ካምፓኒዎች መካከል የሚጠቀስና በርካታ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያለው የኢንቨስትመንት ተቋም ሲሆን ከሀይል ማመንጫ ግንባታዎች በተጨማሪ በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቤቶች ግንባታና በሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ ተቋም ነው፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *