የአፍሪካ የንግድ ፋይናንስን ለማሳደግ የሚያስችል 300 ሚሊየን ዶላር ብድር ከቻይና ተገኘ

የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ከቻይና ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ ጋር የ300 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል።

ስምምነቱ በግብፅ ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን እንደተፈረመ ነው የተነገረው።

ብድሩ በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለውን የጥሬ ዕቃና የአገልግሎት ዘርፍን የበለጠ በማሳለጥ በአፍሪካ ውስጥ የንግድ ፋይናንስና ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ ወሳኝነት እንዳለው ተገልጿል።

በተጨማሪም በአፍሪካ እየጨመረ ያለውን የንግድ ፋይናንስና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ እድገትንና ልማትን ለማጎልበት ያግዛልም ነው የተባለው።

በሦስት ዓመት የሚከፈለው የ300 ሚሊየን ዶላር ብድሩ ኮርፖሬሽኑ ከባንኩ ጋር ባለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት ውስጥ የተገኘ እንደሆነም ከአፍሪካ ኒውስ ሩም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሁለቱ ተቋማት ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ ተባብረው እየሰሩ ሲሆን፥ ኮርፖሬሽኑ እስካሁን 400 ሚሊየን ዶላር የሁለትዮሽ ብድር ከባንኩ ማግኘቱም ነው የተነሳው።

በእስያ ትላልቅ ገበያዎች ላይ አሻራችንን ማሳረፍ መቀጠላችን ለኮርፖሬሽኑ ከባንኩ ጋር ያለው ትብብር ትልቅ ምዕራፍ ነው ያሉት የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የቦርድ አባልና የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ ሳንጄቭ ጉፕታ ናቸው።

በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር በአህጉሪቱ የንግድ ፋይናንስ መፍትሄዎችን ለማቅረብ አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል ብለዋል።

የቻይና ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዌንካይ ዣንግ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ የሁለትዮሽ ትብብራችንን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ እንደሆነና የቻይና አፍሪካን ንግድና ኢኮኖሚ ትብብርን የበለጠ ያሳድጋል ነው ያሉት።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *