የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት መፈጸም ሊጀመር ነው፡፡

አዲስ አበባ 24/6/2015(ንቀትሚ) የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት መፈጸም እንደሚጀመር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትሮች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከለውጡ ማግስት መንግስት ካከናወነው በርካታ የሪፎርም ተግባራት አንዱ የነዳጅ ሪፎርም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግስት ይህንን ሪፎርም ለማድረግ የተገደደው በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሳ በኮንትሮባንድ መልኩ ወደ ውጭ እየተሸጠ መሆኑ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ በተደረገው የሪፎርም ስራም እምርታዎች መታየታቸውን አቶ ገብረ መስቀል ጠቁመዋል፡፡

የነዳጅ ሪፎርሙ ሌላው አላማ ዋጋውን ወደ ትክክለኛ ዋጋ የመውሰድ፣ግብይትና ስርጭቱን ማስተካከል መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ የነዳጅ ምርት የግብይት ስርአቱን ጤናማ እንዲሆን የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው ተግባር በመሆኑ እስከ አሁን 1 ሺህ 26 ማደያዎች ወደ ቴሌብር አሰራር መግባታቸውንም አንስተዋል፡፡

የነዳጅ የግብይት ስርዓቱን በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት የሚከናወን በመሆኑ ማደያዎች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው መንግስት ጠንካራ የትራንስፖርት ፖሊሲ በማዘጋጀት ዓለም ዓቀፋዊ ስትንዳርድን የጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የክፍያ ስርአቱ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ አለመሆን የድጎማ ስርአቱ ላይ ችግር መፍጠሩን እና ለቁጥጥርም አስቸጋሪ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር አለሙ ይህንንም ለመፍታት የነዳጅ ግብይቱን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርአት መፈጸም አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ገልጸዋል።

መንግስት እስካሁን ለነዳጅ ድጎማ 7.3 ቢሊየን ብር መክፈሉም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *