የህንድ ባለሀብቶች በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

በፋርማሲዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩ የህንድ ባለሀብቶች በ279 ሄክታር መሬት ላይ ባረፈው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተሰማርተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።

ባለሀብቶቹ ፍላጎታቸውን የገለፁት የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ልማት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችና ማበረታቻዎችን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች ከቀረቡላቸውና ፓርኩን ከጎበኙ በኋላ ነው ተብሏል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ከባለሀብቶቹ ጋር ውይይት ማካሄዳቸውም ተገልጿል።

አቶ ዘመን ጁነዲን በወቅቱ÷ ኢትዮጵያ ለፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን በተለየ ሁኔታ ለዘርፉ ማመቻቸቷን ተናግረዋል።

የህንድ ባለሀብቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው÷ ኮርፖሬሽናቸው በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የህንድ ባለሀብቶችም በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችንና የአገልግሎት አሰጣጥን ተመልክተው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ በፓርኩ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጀ ያመላክታል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *