እንግሊዝ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራች ነው – አምባሳደር ዳረን ዌልች

ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን የእንግሊዝ እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት በኢንቨሰትመንት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ገለጹ።

አምባሳደር ዳረን ዌልች÷ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት ታሪካዊ በሚባለው በዚሁ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በመልካምም ሆነ በአስቸጋሪ ወቅቶች በጥሩ ወዳጅነትና ጠንካራ ትብብራቸው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ÷ ግንኙነቱ በበርካታ መስኮች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ይህም አጋርነት አሁን ላይ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው÷ በቀጣይም የትብብር አድማሱን በማስፋት ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አገራቸው ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል።

ይሄንንም እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ እድሎች መኖራቸውን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

”በቀጣይ ኢትዮጵያ ትልቋ የልማት አጋራችን ትሆናለች” ያሉት አምባሳደሩ እንግሊዝ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምጣኔዋን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ለማቀላጠፍ በተለይም በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራ ምቹነትን የሚያሳድጉ የማሻሻያ ሥራዎችን ለመደገፍ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።

በሌሎች የልማት መስክ በተለይም በጤና፣ ትምህርትና ሰብዓዊ ጉዳዮች አገራቸው ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *