7 ሚሊዮን ብር ወጭ የወጣው ለሰባት ወራት የሪብራንዲግ ሥራም ጭምር ነው፦ ዓባይ ባንክ

በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ ላለፉት 13 ዓመታት “ዓባይ ታማኝ አገልጋይ” በሚል መሪ ቃል በባንክ አገልግሎት ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የቆየው ዓባይ ባንክ አክሲዮን ማህበር፤ ሰሞኑን “ቀየርኩት” ባለው የንግድ ምልክት መለያ (ሎጎ) የብዙዎች መነጋገርያ ሆኗል።

የዓባይ ባንክ አክሲዮን ማህበር የስትራቴጂክ ዋና መኮንን የሆኑት አቶ ወንድይፍራው ታደሰ አዲሱን መለያ (ሎጎ) በሚመለከት ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሲመሰረት 25 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል ይዞ የነበረው ባንኩ፤ አሁን ላይ 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን የተከፈለ ካፒታል እንዳለው ገልጸዋል።

አጠቃላይ ሀብቱም 60 ቢሊዮን መድረሱን እና 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራቱንም ተናግረዋል።

የስትራቴጂክ ዋና መኮንኑ አቶ ወንድይፍራው እንደሚሉት ይህን እድገት ይበልጥ ለማስቀጠል ከነበረው ሎጎ የተሻለ ለወደፊት ከባንኩ ጋር አብሮ የሚጓዝ ትርጉም እና ፍልስፍና ያለው፤ በቀላሉ የሚታወቅ መለያ ሊኖረው ይገባል ተብሎ ታምኖበት ለ7ወራት የሪብራንዲንግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የባንኩ መነሻ የሆነውን የታላቁን የዓባይ ወንዝ ስም፣ ባህርይ፣ ግዝፈት የሚያመላክት ለገበያው ምቹ እና ፈጣን የሚለውን ተሳቢ በማድረግ አዲስ መለያ ሎጎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የዓባይ ባንክ አክሲዮን ማህበር የስትራቴጂክ ዋና መኮንን አቶ ወንድይፍራው ታደሰ እንደሚሉት “የዓባይ ወንዝ በጭስ ዓባይ ፏፏቴ ላይ ሲፈስ በጉልህ የሚታዩትን ሰባት መስመሮች በመምረጥ የመለያ ምልክት አድርገነዋል። ይህም ሰባት ቀናት ሃያ አራት ሰዓት አገልጋይነታችንን ገላጭ ነው።” ብለዋል።

ይህን መለያ ሎጎ ለመስራት 7 ሚሊዮን ብር ወጭ መሆኑን በተመለከተም አቶ ወንድይፍራው ሲገልጹ፤ የወጣው ለሎጎው ብቻ ሳይሆን ሰባት ወራትን ለፈጀው አጠቃላይ የሪብራንዲግ ስራ ነው። በማለት ገልጸዋል።

በቀጣይ ባንኩ የሚታወቅበትን “ዓባይ ታማኝ አገልጋይ” የሚለው መሪ ቃሉንም አሻሽሎ እንደሚመጣ ኃላፊው ተናግረዋል።

ዓባይ ባንክ አክሲዮን ማህበር አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ 527 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፤ በሳለፍነው ቅዳሜ ካስተዋወቀው አዲስ ሎጎ ጋር አዲስ የድረ_ገፅ እና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

Source: EBC

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *