የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍተሻ ኬላዎች በፍጥነት ለማለፍ የሚያስችለው የቲኤስኤ አጋር ሆነ

በአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ቡድን የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከአሜሪካ የትራንስፖርት ደህንነት አስተዳደር (ቲኤስኤ) ፕሮግራም ጋር በአጋርነት መሥራት መጀመሩን አብስሯል።

ፕሮግራሙ ጫማዎችን፣ ላፕቶፖችን፣ ፈሳሾችን፣ ቀበቶዎችን እና ቀላል ጃኬቶችን ሳያወልቁ ተሳፋሪዎች በደህንነት ማጣሪያው ተፈትሸው የሚያልፉበትን ወሳኝ አገልግሎቶችን ይሰጣል።

መርሃ ግብሩ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ የአየር መንገዱ ደንበኞች ጫማቸውን፣ ቀበቷቸውን እና ቀላል ጃኬቶቻቸውን እንዲሁም ላፕቶፖችን እና የ3-1-1 ፈሳሾች አያያዝ ሥርዓትን የሚከተል እንደሆነ ተነስቷል፡፡

በዚህም መንገደኞች የተሻለ ጉዞ ለማድረግ እንከን የለሽ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የሆነ የደህንነት ማጣሪያ መፍትሄ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።

የ3-1-1 ፈሳሾች ህግ ተሳፋሪዎች እያንዳንዳቸው 100 ሚሊ ሜትር የሆነ በጉዞ ወቅት ፈሳሾችን፣ ጄል እና ኤሮሶሎችን መያዝ የሚያስችል የቲኤስኤ ደንብ መሆኑ ተመላክቷል።

ይህ ደንብ የደህንነት ሂደቱን የሚያመቻች እና በአየር መንገድ የፍተሻ ኬላዎች በፍጥነት ለማለፍ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አጋርነቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ይህ ትብብር በ25 ዓመታት የአሜሪካ አገልግሎት ታሪካችን ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

ለመንገደኞችም በተፋጠነ የደህንነት ቁጥጥር ጉዞ የማድረግ ልምድን እንደሚያሳድግ ገልፀው÷ ከቲኤስኤ ፕሮግራም ጋር ያለን ውህደት ከተጨማሪ ምቾት በላይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ይህንን የተፋጠነ አገልግሎት በአሜሪካ ከሚገኙ አምስት ቁልፍ መዳረሻዎች ማለትም ከአትላንታ፣ ቺካጎ፣ ኒዋርክ፣ ኒውዮርክ እና ዋሽንግተን ለሚጓዙ ደንበኞቹ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።

የአሜሪካ ዜጎች ወይም ህጋዊ ቋሚ ነዋሪ የሆኑ ደንበኞች በቲኤስኤ ቅድመ ማጣሪያ ማመልከቻ ፕሮግራም ሦስት ፍቃድ ከተሰጣቸው የምዝገባ አቅራቢዎች በአንዱ በመመዝገብ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *