የቡድን 77 እና የቻይና የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ

ለሁለት ቀናት በኩባ ሀቫና ሲካሄድ የቆየው የቡድን 77 እና የቻይና የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት የደቡብ ንፍቀ ዓለምን ፍላጎት የሚያስተናግድ እውነተኛ ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በተናጠል የሚጣሉ ማዕቀቦችና ኃይልን መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ እርምጃዎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ልማት ለውጦችን እንደሚያስተጓጉሉም ገልጸዋል።

በደቡብ-ደቡብ የትብብር መድረክ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ ፈጠራን ለማሳደግና ለዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እየተገበረች ባለው የዲጂታል ስትራቴጂ ለሰፊው ማህበረሰብ ሰፊ ጥቅሞችን መስጠት የሚችል ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመፍጠር ራዕይ ሰንቃ እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ስትራቴጂውን በመተግበር አበረታች ውጤቶችን እያገኘች መሆኑን ነው አቶ ደመቀ ያስረዱት።

ኢትዮጵያዊ በጉባኤው በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ስኬታማ ስራ ማከናወኗም ተገልጿል።

በኩባ የተካሄደው ጉባኤ በማጠናቀቂያው የአቋም መግለጫ ማውጣቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ምንጭ፦ ኢ.ፕ.ድ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *