ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሥራ ፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል ጀመረ

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሥራ ፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል መጀመሩን አስታውቋል።

ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ፥ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ ቁ.01/2016 መሠረት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት የሚፈልጉ የሥራ ፈቃድ ማመልከቻ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።

በገበያ ላይ ተመሥርተው የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መሸጥና መግዛት የሚፈልጉ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲቋቋሙ በተፈቀደው መሠረት የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ እንዲሁም የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ቢሮ መስፈርቱን አሟልተው ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ሲያገኙ መክፈት እንደሚችሉም አስገንዝቧል።

የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመከፈት የሚያስፈልገውየካፒታል መጠን እንዲሁም ሌሎች ለሥራው የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ከባንኩ ድረ ገጽ መመልከት እንደሚቻል ባንኩ ጠቁሟል።

የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መቋቋም የውጭ ምንዛሪ ገበያን መሠረት ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት የሚሹ ደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት እንደሚረዳም በመግለጨው አውስቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ባስተላለፉት መልእክት፥”የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ የሥራ ፈቃድ መስጠታችን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ለመክፈትና ዘርፉን በቀጣይ ዓመታት ከዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችና አሠራሮች ጋር የተመጣጣነና ተወዳዳሪ ለማድረግ የጀመርነውን አዲስ ምዕራፍና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን ስትራቴጂካዊ ለውጥ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት መነሣሣቱን የሚያመለክት ነው” ብለዋል።

ምንች፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *