የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ አበረታታለሁ – ሚኒስቴሩ

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተለያዩ የማበረታቻ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሐሰን ገለጹ።

በዚሁ መሠረት፣ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚከፈለው ታክስ 15 በመቶ እና በከፊል ተገጣጥመው ለሚገቡ ደግሞ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችም ከታክስ ነጻ መደረጋቸውንም አስረድተዋል።

ይህም በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ከሚጣለው ታክስ አንጻር አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት እየሠራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የጥገና ማዕከል እና የቻርጅ ስቴሽን እጥረት እንዳይኖር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ላይ በአዲስ አበባ 60 የቻርጅ ስቴሽኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በ10 ዓመትም በአዲስ አበባ 1 ሺህ 176 እንዲሁም በክልል ከተሞች 1 ሺህ 50 የቻርጅ ስቴሽኖችን ለመሥራት ታቅዷል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

439 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በ10 ዓመት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *