የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት አሳዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎታቸውን ገለጹ፡፡

የኢትዮ- ሰካሪያ / ቱርክ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ፎረም ጳጉሜ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በሰካሪያ መካሄዱ ይታወሳል።

በፎረሙ ለተጨማሪ ውይይት 14 ባለሀብቶች በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ አደም መሐመድ÷በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጎት በማሳየታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አማራጮች እና በኢትዮጵያ በቀጣይ ሊዘጋጁ ስለ ታሰቡ የንግድ አውደ ርዕይዎች አስመልክቶ አምባሳደር አደም መሐመድ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለሀብቶቹ በበኩላቸው÷በቱርክ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለነዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሆነ በማንሳት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በቴክስታይል ፣ በኢነርጂና በንግድ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ ወራት ለቅደመ ኢንቨስትመንት ጥናት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት እንዳላቸውም መናገራቸውን ከቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *