የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለኢንዱስትሪ ልማት በቂ የሰው ሀይል እንዳለው ተገለፀ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለኢንዱስትሪ ልማት የሚሆን በቂ የሰው ሀይልና የከተሜነት ምጣኔ አለው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው ተናገሩ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና የተኪ ምርት ስትራቴጂ ዙሪያ በሆሳዕና ከተማ  ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው÷ የኢንዱስትሪ ፖሊሲና የተኪ ምርት ስትራቴጂ ጉዳዮች ለክልሉ እድገት ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ክልሉ ከፍተኛ የከተሜነት ምጣኔ፣ በቂ የሰው ሃይል ያለበትና ከማዕከል ቅርብ በመሆኑ ለኢንዱስትሪም ሆነ ለግብርናው መስክ አምራች ዘርፍ ምቹና ተመራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው÷ የሀገራችን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ባለሀብቱን፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ ሰፊውን የሰው ሀይልና የመንግሥትን ቁርጠኛ አመራር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኢንቨስትመንት፣ በተኪና ተወዳዳሪ ኤክስፖርት ምርት፣ የውጭ ገበያ ድርሻን በማስፋት እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ለዘርፉ ምቹ ከባቢ መፍጠር፣ ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓትና አገልግሎት መዘርጋትና በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንዲሁም የሰው ሃይልን ሁነኛ የኢንዱስትሪ ግብዓት አድርጎ መጠቀም ላይ ፖሊሲው ትልቅ ቦታ መስጠቱን አብራርተዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *