ኮሚቴው የቻይና ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲያመርቱ ጥረት እንደሚያደርግ ገለጸ

ቻይናውያን ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ማምረት እንዲችሉ እንደሚሠራ የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ኮርፖሬሽን ኮሚቴ አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ከኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ኮርፖሬሽን ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቤቲ ዡ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም፣ በኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ኮርፖሬሽን ስር የሚገኙ አምራች ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው እንዲያመርቱ ሊከናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ ለአምራቾች የተዘጋጁ ምቹ መሰረተ ልማቶችን እና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን አቶ አክሊሉ አብራርተዋል።

ቤቲ ዡ በበኩላቸው ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ማምረት እንዲችሉ እንደሚሠሩ ገልጸው፣ ለዚህም በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ኮርፖሬሽን ስር በአውቶሞቢል፣ በማሽነሪ፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር እና ሌሎችም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ከ100 በላይ ቻይናውያን አምራች ባለሃብቶችን መኖራቸውን እንደገለጹ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።

ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የኢንቨስትመንት ፎረም በቻይና ለማዘጋጀት ከስምምነት መደረሱም ተገልጿል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *