ከወርቅ ምርት 63 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መገኘቱ ተገለጸ

በ2016 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወርቅ ምርት 63 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማዕድን ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል።

በሩብ ዓመቱ 996 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ታቅዶ 719 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም በኩባንያዎች ተመርቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ተናግረዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታና የመሰረተ ልማት ችግር መኖር የሚፈለገውን ውጤት እንዳይመዘገብ ማድረጉንም አስገንዝበዋል።

በኩባንያ ደረጃ ያለው የወርቅ ምርት አፈጻጸም 78 በመቶ እንዲሁም በባህላዊ የወርቅ ምርት ያለው አፈጻጸም 22 በመቶ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

በሩብ ዓመቱ ከወርቅ ምርት 112 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 63 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መገኘቱንም ገልጸዋል።

አፈጸጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የተሻለ ቢሆንም ከዕቅዱ አንጻር ግን ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና መሰረታዊ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በያዝነው በጀት ዓመት ከወርቅ፣ ከከበሩ ድንጋዮች፣ ከሊቲየምና ሌሎች ዘርፎች 512 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *