ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ተፈራርመው ወደ ስራ ያልገቡ ኩባንያዎች ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ተገለጸ

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ውል ተፈራርመው ወደ ስራ ያልገቡ ሀገር በቀልና የውጭ ኩባንያዎች እንዲሁም ባለሀብቶች በአፋጣኝ ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ አሳሰቡ።

አቶ አክሊሉ ታደሰ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ከፈፀሙ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ጋር ተወያይተዋል።

ውል ተፈራርመው የማምረቻ ሼድና የለማ መሬት ወስደው ግንባታና ማሽን ተከላ የጀመሩትን በመደገፍ ወደ ማምረት ሂደት እስከሚገቡ ድረስ ኮርፖሬሽኑ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በሙሉ አቅም ወደ ምርት ሂደት የገቡትን ደግሞ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ገበያዎችን በማፈላለግ ጭምር ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አመላክተዋል።

በመድረኩ የኮርፖሬሽኑ ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች እና የኢንቨስትመንት ፍሰት መረጃዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸውም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።

የውይይቱ አላማ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ተዋውለው በአጭር ጊዜ ወደ ግንባታና የምርት ሂደት የገቡትን ለማበረታታትና ወደ ተግባር ያልገቡትን በመለየት ለመደገፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በቀጣይም መሰል መድረኮች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትና ባለሃብቶች በሚገኙበት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *