የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባለኃብቶች በሻይ ቅጠል ምርት በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ።
ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ወደ ሥራ የተገባው የሻይ ቅጠል ምርትን የማስፋት ሥራ ጥሩ ጅማሮ ማሳየቱ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ሦስት ዓመት በሻይ ቅጠል ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችውን ኬንያን ከጎበኙ በኃላ ተሞክሮውን ለማስፋት በስፋት እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ምርቱን ለማስፋት 460 ሚሊየን ችግኝ አባዝቶ በተያዘው በጀት ዓመት 30 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የሻይ ቅጠል ምርት መተከሉን ለኢዜአ ገልፀዋል።
በአገራችን በቀዳሚነት ተጠቃሽ የሆነው የውሽውሽና ጉመሮ ምርት በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ያረፈ እንደነበረም ነው የተገለፀው።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት 11 ወራት 950 ቶን በአግባቡ የተዘጋጀ የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ብቻ ተገኝቷል።
ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ50 ሺህ ቶን ብልጫ ቢኖረውም አገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።
ባለኃብቶች በዘርፉ በስፋት ባለመሳተፋቸው ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ኃብት አንጻር ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እንዳታገኝ እንቅፋት ሆኖባታል ተብሏል።
እስካሁን ከሻይ ቅጠል የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በዓመት ከ3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አለመብለጡንም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ለሻይ ምርት ምቹ የሆነ የአየር ጸባይና የአፈር ሁኔታ ያላት አገር መሆኗን ጠቁመው፤ የሻይ ቅጠል ምርት አሲዳማና ተዳፋት በሆኑ መሬቶች ላይ ጭምር መብቀል የሚችል በመሆኑ ምርቱን ለማስፋት አርሶ አደሩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
የሻይ ምርት በአርሶ አደሩ ብቻ የሚሰፋ ባለመሆኑ ባለኃብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስትም በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሃብቶች የተለያያ ማበረታቻዎች እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሻይ ቅጠል ምርት አንድ ጊዜ ከተተከለ ለ30 እና 40 ዓመታት ምርቱ የሚቆይና በየ15 ቀኑ ምርቱን በመቅጠፍ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ነው።
ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ሌሎች ክልሎችም የሻይ ምርትን ለማስፋት በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ 99 በመቶ የሚሆነውን የሻይ ምርት ወደ እንግሊዝ ትልካለች።
ምንጭ፦ ኢዜአ