ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቡና ንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደምትፈልግ ገለጸች

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቡና ንግድ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዱ ጂሃኦ ገለጹ።

በቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶና ሌሎች የምክር ቤት አባላት ገላን የሚገኘውን ኤ ኤም ጂ ቡና ላኪ ድርጅትን ጎብኝተዋል።

ዱ ጂሃኦ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ገበያ በስፋት እየታወቀ ነው።

የቻይና ባለሃብቶች በቡና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በኢትዮጵያ መኖሩን መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።

ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱና የኢትዮጵያ ቡና በብዛት እና በጥራት ተመርቶ በስፋት ለዓለም ገበያ መቅረብ እንዲችል የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት ቡናን በጥራትና በብዛት ማቅረብ ከቻለች የገበያ ዕድሉ በቻይና መኖሩንም ነው ያስረዱት።

በአሁኑ ወቅትም በቻይና ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ቀደም ብሎ የነበረውን ሻይ የመጠጣት ባህሉን ወደ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህን የተረዱ የቻይና የቡና ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና እየገዙና የንግድ ትስስር እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

ይህን ለማጠናከርም ቋሚ ከሚቴው ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመቀራረብ ይሠራል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን ቡና በጥራትና በብዛት በማምረት ከምትልክባቸው ቀዳሚ ሀገራት ቻይና አንዷ መሆኗን ገልፀዋል።

ለአብነትም ወደ ቻይና በ2015 ዓ.ም 10 ሺህ 879 ቶን ቡና ተልኮ 70 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በ2016 የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመትም 2 ሺህ 285 ቶን ቡና መላኩን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በጥራትና በብዛት እያመረተች መሆኑን አስረድተው÷ የቡና ገበያ በቻይና እንዲሰፋ ጠይቀዋል።

የቻይና ባለሃብቶችም በቡና ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ መሰማራት መጀመራቸውን ገልጸው÷ ይህን ተግባራቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *