ቻይና በዓለም አቀፍ የመርከብ ግንባታ ዘርፍ ቀዳሚነቷን አረጋገጠች

ቻይና በዓለም አቀፍ የመርከብ ግንባታ ዘርፍ ለ14 ተከታታይ ዓመታት በቀዳሚነት መቀጠሏ ተገለጸ።

ቻይና ባለፈው ዓመት ውስጥ በምርታማነት፣ በአዳዲስ ትዕዛዞች እና ቀደም ብለው በተሰጡ ትዕዛዞች ጠንካራ እድገት እያሳየች መምጣቷን አስመስክራለች ተብሏል።

በእነዚህ ሦስት ዋና ዋና አመላካቾችም በዓለም አቀፍ የመርከብ ግንባታ ገበያ ውስጥ ለ14 ተከታታይ ዓመታት የመሪነቱን ሥፍራ መያዟን የኢንዱስትሪ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ቻይና በሦስቱ አመላካቾች ሁሉን አቀፍ እድገት በማስመዝገብ በዓለም ብቸኛዋ ሀገር መሆኗም ተገልጿል።

ባለፉት 12 ወራት የቻይና የመርከብ ግንባታ ምርት 42 ነጥብ 32 ሚሊየን ቶን እንደደረሰና ከዓመት ዓመትም የ11 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መሆኑ ተመላክቷል።

ይህም ከዓለም አጠቃላይ የምርት ዕድገት 50 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ እንዳለው ነው የተገለጸው።

አዳዲስ ትዕዛዞችም ከዓመት ወደ ዓመት በ 56 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ እንዳሉና የምርት ሂደቱም ወደ 71 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን አጠቃላይ ክብደት እንዳደገ ተጠቁሟል።

ይህም ከዓለም አጠቃላይ ምርት 66 ነጥብ 6 በመቶውን እንደሚይዝ ነው የተመላከተው።

በታህሳስ ወር መጨረሻ፣ በእጅ ያለው የትዕዛዝ መጠን 139 ነጥብ 39 ሚሊየን የተጣራ ክብደት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በዓመትም 32 በመቶ ጨምሯል መባሉን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።

በፈረንጆቹ 2023 አምስት የቻይና የመርከብ ግንባታ ኢንተርፕራይዞች በምርታማነት፣ ሰባቱ በአዳዲስ የትዕዛዝ መጠን እንዲሁም ስድስቱ ደግሞ ቀደም ብለው በተሰጡ ትዕዛዞች በዓለም ምርጥ 10 ውስጥ መካተታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ማመላከቱን ዘገባው አያይዞ ገልጿል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *