በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑክ በሻንጋይ ከተማ የስራ ጉብኝት አደረገ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ የቻይና የንግድ ማዕከል በሆነችው በሻንጋይ ከተማ የስራ ጉብኝት እና ውይይት አድርጓል።

በጉብኝቱ ከከንቲባ አዳነች በተጨማሪ ም/ከንቲባ ጃንጥራር አባይና ሌሎች የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ልዑካን ቡድኑ ከጉብኝት ጎን ለጎን በዘመናዊ የከተማ መዋቅራዊ ፕላን እና አተገባበር፣ በመሰረተ ልማት ቅንጅትና ግንባታ፣ በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር እንዲሁም ዘመናዊ ከተማ መገንባት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ከሻንጋይ ከተማ ፕላን እና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

በተጨማሪም÷ የቻይና የንግድ ማዕከል የሆነችው የሻንጋይ ከተማ በምትታወቅበት ዲጂታላይዝድ አገልግሎቶችና በስማርት ሲቲ ግንባታ ሂደት ለኢትዮጵያ ከተሞች ልምድ በምታጋራበትና አብሮ መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መምከራቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *